መልካም ስነ ምግባር


11 Aug
11Aug

ስነ ምግባር በእስልምና ከፍተኛ ስፍራ ተሰጥቶታል፡፡ የአላህ መልእክተኛ የተላኩበትን ዓይነተኛ ዓላማ፣ የዳዕዋቸውን ጉልህ ሚና እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፡-

‹‹እኔ የተላክኩት መልካም ስነ ምግባራትን ለመሙላት ነው፡፡››

አላህ እርሳቸውን ሲያሞግስ እንዲህ ብሏል፡-

وَإِنَّكَ لَعَلَىٰ خُلُقٍ عَظِيمٍ

‹‹አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡›› (አል ቀለም 4)

ሙስሊሞች ከዓለም መሪነት ሚናቸው የተወገዱት ኢስላም ካመጣው መልካም ስነ ምግባር ርቀው በልዋጩ አንዴ የምእራቡን፣ ሌላ ጊዜ የምስራቁን እሴቶች በማማተራቸው ነው፡፡

ከአላህ መልእክተኛ ትምህርት በጥቂቱ

ኡሳማ ቢን ሸሪክ እንዲህ ሲል አስተላልፏል፡-

ከአላህ መልእክተኛ ዘንድ፣ ከራሳችን ላይ በራሪ ያረፈ ያህል አንገታችንን ደፍተን በጽናት ተቀምጠን እያለ ሰዎች መጡና፡-

‹‹ከአላህ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ የሆኑ የአላህ ባሮች እነማን ናቸው?›› ሲሉ ጠየቋቸው፡፡ ‹‹ስነ ምግባራቸው የበለጠ መልካም የሆነው›› በማለት መለሱ፡፡ (ጦበራኒ)

በሌላ ዘገባ፡- ‹‹የሰው ልጅ ከሚታደላቸው  ስጦታዎች ሁሉ በላጩ የትኛው ነው?›› ሲሉ ጠየቁ፡፡ ነቢዩም፡- ‹‹መልካም ስነ ምግባር›› በማለት መለሱ፡፡ (ቲሚዚ)

የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹ብልግና መናገርና መፈጸም የእስልምና አካል አይደለም፡፡ ከሰዎች መካከል እስልምናው ይበልጥ ያማረው በስነ ምግባር በላጬ ነው፡፡›› (ቲርሚዚ)

አብደላህ ቢን ዓምር እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ፡-

‹‹ከኔ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅና በእለተ ቂያማም ለኔ ይበልጥ የቀረበ ማረፊያ የሚኖረው ሰው ማን እንደሆነ ልንገራችሁን?›› በማለት ሁለት

ወይም ሦስት ጊዜ ደጋግመው ጠየቁ፡፡ ‹‹አዎ›› አሏቸው፡፡ ‹‹ስነ ምግባሩ ይበልጥ ያማረው ሰው ነው፡፡›› ሲሉ መለሱ፡፡ (አህመድ)

የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡-

‹‹በእለተ ቂያማ ከሙእሚን ሚዛን ላይ ከመልካም ስነ ምግባር የሚከብድ ነገር የለም፡፡ አላህ ባለጌን አይወድም፡፡ የልካም ስነ ምግባር ባለቤት ጿሚዎችና ሰጋጆች ከሚደርሱበት ደረጃ ይደርሳል፡፡›› (አህመድ)

Comments
* The email will not be published on the website.